Proverbs 24

1በክፉ ሰዎች አትቅና፤
ጓደኝነታቸውም አይመርህ፤
2ልባቸው ዐመፅን ያውጠነጥናልና፤
ከንፈራቸውም ሸፍጥ ያወራል።

3ቤት በጥበብ ይሠራል፤
በማስተዋልም ይጸናል፤
4በዕውቀትም ውድና ውብ በሆነ ንብረት፣
ክፍሎቹ ይሞላሉ።

5ጠቢብ ሰው ታላቅ ኀይል አለው፤
ዕውቀት ያለውም ሰው ብርታትን ይጨምራል፤
6ጦርነት ለመግጠም መልካም ምክር፣
ድል ለማድረግም ብዙ አማካሪዎች ያስፈልጋሉ።

7ጥበብ ለተላላ በጣም ሩቅ ናት፤
በከተማዪቱ በር ሸንጎ ላይም መናገር አይችልም።

8ክፋት የሚያውጠነጥን፣
“ተንኰለኛ” በመባል ይታወቃል።
9የተላላ ዕቅድ ኀጢአት ነው፤
ሰዎችም ፌዘኛን ይጸየፋሉ።

10በመከራ ጊዜ ፈራ ተባ ካልህ፣
ዐቅምህ ምንኛ ደካማ ነው!

11ወደ ሞት የሚነዱትን ታደጋቸው፤
እየተጐተቱ ለዕርድ የሚሄዱትን አድናቸው።
12አንተም፣ “ስለዚህ ነገር ምንም አላውቅም” ብትል፣
ልብን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን?
ሕይወትህን የሚጠብቃት እርሱ አያውቅምን?
ለእያንዳንዱስ እንደ ሥራው መጠን አይከፍለውምን?

13ልጄ ሆይ፤ መልካም ነውና ማር ብላ፤
የማር ወለላም ጣዕም ይጣፍጥሃል።
14ጥበብም ለነፍስህ እንደዚሁ ጣፋጭ እንደ ሆነች ዕወቅ፤
ብታገኛት ለነገ አለኝታ ይኖርሃል፤
ተስፋህም ከንቱ አይሆንም።

15በጻድቅ ሰው ቤት ላይ እንደ ወንበዴ አታድፍጥ፤
መኖሪያውንም በድንገት አታጥቃ፤
16ጻድቅ ሰባት ጊዜ እንኳ ቢወድቅ ይነሣልና፤
ክፉዎች ግን በጥፋት ይወድቃሉ።

17ጠላትህ ሲወድቅ ደስ አይበልህ፤
ሲሰናከልም ልብህ ሐሤት አያድርግ፤
18አለዚያ እግዚአብሔር ይህን አይቶ ደስ አይለውም፤
ቍጣውንም ከእርሱ ይመልሳል።

19በጨካኞች ድርጊት አትጨነቅ፤
በክፉዎችም አትቅና፤
20ግፈኛ ተስፋ የለውምና፤
የክፉዎችም መብራት ድርግም ብላ ትጠፋለች።

21ልጄ ሆይ፤ እግዚአብሔርንና ንጉሥን ፍራ፤
ከዐመፀኞችም ጋር አትተባበር፤
22ሁለቱም የሚያመጡት መዓት፤
ምን እንደሚሆን ማን ያውቃል?

ተጨማሪ የጠቢባን ምሳሌዎች

23እነዚህም ደግሞ የጠቢባን ምሳሌዎች ናቸው፦

በዳኝነት አድልዎ ማድረግ ተገቢ አይደለም፤
24በደለኛውን፣ “አንተ ንጹሕ ነህ” የሚለውን፣
ሕዝቦች ይረግሙታል፤ መንግሥታትም ያወግዙታል።
25በደለኛውን፣ “አንተ ጥፋተኛ ነህ” የሚሉት ግን መልካም ነገር ይገጥማቸዋል፤
የተትረፈረፈ በረከትም ይወርድላቸዋል።

26እውነተኛ መልስ መስጠት፣
ከንፈርን እንደ መሳም ነው።

27በደጅ ያለውን ሥራህን ፈጽም፤
ዕርሻህን አዘጋጅ፤
ከዚያም በኋላ ቤትህን ሥራ።

28በባልንጀራህ ላይ ያለ ምክንያት አትመስክር፤
በከንፈርህም አትሸንግል።
29“በእኔ ላይ እንደ ሠራብኝ እሠራለታለሁ፤
ስለ አድራጎቱም የእጁን እመልስለታለሁ” አትበል።

30በሰነፍ ሰው ዕርሻ በኩል ዐለፍሁ፤
ማስተዋል የጐደለውን ሰው የወይን ቦታ ዐልፌ ሄድሁ፤
31በያለበት እሾኽ በቅሎበታል፤
መሬቱም ዐረም ለብሷል፤
ቅጥሩም ፈራርሷል።
32ያየሁትን ነገር አወጣሁ፣ አወረድሁ፤
ካስተዋልሁትም ትምህርት አገኘሁ፤
33“ጥቂት ላንቀላፋ፣ ጥቂት ላሸልብ፣
እጄን አጣጥፌ ጥቂት ልረፍ” ብትል፣
34ድኽነት እንደ ወንበዴ፣
ዕጦትም እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል።
ወይም እንደ ቦዘኔ ወይም ዕጦትም እንደ ለማኝ

Copyright information for AmhNASV